islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


የአንዱን ወር ክብር ወደ ሌላው ማዘግየት በክህደት ላይ (ክህደትን) መጨመር ብቻ ነው፡፡ በእርሱ እነዚያ የካዱት ሰዎች ይሳሳቱበታል፡፡ በአንድ ዓመት የተፈቀደ ያደርጉታል፡፡ በሌላው ዓመትም ያወግዙታል፡፡ (ይህ) አላህ ያከበራቸውን ወሮች ቁጥር ሊያስተካክሉ፣ አላህም እርም ያደረገውን የተፈቀደ ሊያደርጉ ነው፡፡ የሥራዎቻቸው መጥፎው ለነርሱ ተዋበላቸው፡፡ አላህም ከሓዲያን ሕዝቦችን አይመራም፡፡

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህ መንገድ (ለመታገል) ውጡ በተባላችሁ ጊዜ ወደ ምድር የምትወዘፉት ለእናንተ ምን አላችሁ የቅርቢቱን ሕይወት ከመጨረሻይቱ ይበልጥ ወደዳችሁን የቅርቢቱም ሕይወት ጥቅም በመጨረሻይቱ (አንጻር) ጥቂት እንጂ አይደለም፡፡

ለዘመቻ ባትወጡ (አላህ) አሳማሚን ቅጣት ይቀጣችኋል፡፡ ከእናንተ ሌላ የኾኑንም ሕዝቦች ይለውጣል፡፡ በምንም አትጎዱትምም፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

(ነቢዩን) ባትረዱት እነዚያ የካዱት ሕዝቦች የሁለት (ሰዎች) ሁለተኛ ኾኖ (ከመካ) ባወጡት ጊዜ አላህ በእርግጥ ረድቶታል፡፡ ሁለቱም በዋሻው ሳሉ ለጓደኛው አትዘን አላህ ከእኛ ጋር ነውና ባለ ጊዜ አላህም መረጋጋትን በእርሱ ላይ አወረደ፡፡ ባላያችኋቸውም ሰራዊት አበረታው፡፡ የእነዚያንም የካዱትን ሰዎች ቃል ዝቅተኛ አደረገ፡፡ የአላህም ቃል ለእርሷ ከፍተኛ ናት፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡