islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


ቀላሎችም ከባዶችም ኾናችሁ ዝመቱ፡፡ በአላህም መንገድ በገንዘቦቻችሁ በነፍሶቻችሁም ታገሉ፡፡ ይህ የምታውቁ ብትኾኑ ለናንተ በጣም የተሻለ ነው፡፡

(የጠራህባቸው ነገር) ቅርብ ጥቅምና መካከለኛ ጉዞ በኾነ ኖሮ በተከተሉህ ነበር፡፡ ግን በነሱ ላይ መንገዲቱ ራቀችባቸው፡፡ «በቻልንም ኖሮ ከእናንተ ጋር በወጣን ነበር» ሲሉ በአላህ ይምላሉ፡፡ ነፍሶቻቸውን ያጠፋሉ፡፡ አላህም እነሱ ውሸታሞች መኾናቸውን በእርግጥ ያውቃል፡፡

አላህ ከአንተ ይቅር አለ፡፡ እነዚያ እውነተኛዎቹ ላንተ እስከሚገለጹልህና ውሸታሞቹንም እስከምታውቅ ድረስ ለነርሱ (እንዲቀሩ) ለምን ፈቀድክላቸው

እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑት በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው ከመታገላቸው (ለመቅረት) ፈቃድን አይጠይቁህም፡፡ አላህም የሚፈሩትን ዐዋቂ ነው፡፡

ፈቃድን የሚጠይቁህ እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑት ልቦቻቸውም የተጠራጠሩት ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም በጥርጣሬያቸው ውስጥ ይዋልላሉ፡፡

መውጣትንም ባሰቡ ኖሮ ለርሱ ዝግጅትን ባሰናዱ ነበር፡፡ ግን አላህ (ለመውጣት) እንቅስቃሴያቸውን ጠላ (አልሻውም)፡፡ አሰነፋቸውም፡፡ ከተቀማጮቹም ጋር ተቀመጡ ተባሉ፡፡

ከእናንተ ጋር በወጡ ኖሮ ጥፋትን እንጂ አይጨምሩላችሁም ነበር፡፡ ሁከትንም የሚፈልጉላችሁ ሲኾኑ በመካከላችሁ (በማሳበቅ) ይቻኮሉ ነበር፡፡ በናንተም ውስጥ ለነሱ አዳማጮች አሏቸው፡፡ አላህም በዳዮችን ዐዋቂ ነው፡፡