islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


ወደእነሱ በተመለሳችሁ ጊዜ ምክንያታቸውን ያቀርቡላችኋል፡፡ አታመካኙ፤ እናንተን ፈጽሞ አናምንም፡፡ አላህ ከወሬዎቻችሁ በእርግጥ ነግሮናልና፡፡ አላህም ሥራችሁን በእርግጥ ያያል፡፡ መልክተኛውም (እንደዚሁ)፤ ከዚያም ሩቅንና ቅርብን ሁሉ ዐዋቂ ወደ ኾነው (አላህ) ትመለሳላችሁ ወዲያውም ትሠሩት የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል በላቸው፡፡

ወደእነሱ በተመለሳችሁ ጊዜ እንድትተውዋቸው ለእናንተ በእርግጥ በአላህ ይምላሉ፡፡ እነሱንም ተዋቸው፡፡ እነሱ እርኩሶች ናቸውና፡፡ ይሠሩትም በነበሩት ዋጋ መኖሪያቸው ገሀነም ነው፡፡

ከእነሱ ትወዱላቸው ዘንድ ለናንተ ይምሉላችኋል፡፡ ከእነሱ ብትወዱም አላህ አመጸኞች ሕዝቦችን አይወድም፡፡

አዕራቦች በክህደትና በንፍቅና በጣም የበረቱ፤ አላህም በመልክተኛው ላይ ያወረደውን ሕግጋት ባለማወቅ የተገቡ ናቸው፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡

ከአዕራቦችም (በአላህ መንገድ) የሚወጣውን (ገንዘብ) ዕዳ አድርጎ የሚይዝ በእናንተም ላይ የጊዜን መገለባበጥ የሚጠባበቅ ሰው አልለ፡፡ በእነሱ ላይ ጥፋቱ ይዙርባቸው፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡

ከአዕራቦችም በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን የሚሰጣቸውንም (ምጽዋቶች) አላህ ዘንድ መቃረቢያዎችና ወደ መልክተኛው ጸሎቶች መዳረሻ አድርጎ የሚይዝ ሰው አልለ፡፡ ንቁ! እርሷ ለእነሱ በእርግጥ አቃራቢ ናት፡፡ አላህ በችሮታው ውስጥ (በገነቱ) በእርግጥ ያስገባቸዋል፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡