islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


አላህም ጉዳትን ቢያደርስብህ ከእርሱ ሌላ ለእርሱ ገላጭ የለውም፡፡ በጎንም ነገር ቢሻልህ ለችሮታው መላሽ የለም፡፡ ከባሮቹ የሚሻውን በእርሱ ይለይበታል፡፡ እርሱም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡

«እናንተ ሰዎች ሆይ! እውነቱ ከጌታችሁ በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ (በእርሱ) የተመራም ሰው የሚመራው ለራሱ ነው፡፡ የተሳሳተም ሰው የሚሳሳተው (ጉዳቱ) በራሱ ላይ ነው፡፡ እኔም በእናንተ ላይ ተጠባበቂ አይደለሁም» በላቸው፡፡

ወዳንተም የሚወረደውን ነገር ተከተል፡፡ አላህም (በነሱ ላይ) እስከሚፈርድ ድረስ ታገስ፡፡ እርሱም ከፈራጆቹ ሁሉ በላጭ ነው፡፡

አ.ለ.ረ (አሊፍ ላም ራ፤ ይህ ቁርኣን) አንቀጾቹ በጥንካሬ የተሰካኩ ከዚያም የተዘረዘሩ የሆነ መጽሐፍ ነው፡፡ ጥበበኛ ውስጠ ዐዋቂ ከሆነው ዘንድ (የተወረደ) ነው፡፡

(እንዲህ በላቸው)፡- «አላህን እንጂ ሌላን አትገዙ፡፡ እኔ ለእናንተ ከርሱ (የተላክሁ) አስፈራሪና አብሳሪ ነኝ፡፡»

ጌታችሁንም ምሕረትን ለምኑት፡፡ ከዚያም ወደእርሱ ተመለሱ፡፡ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ መልካምን መጥቀም ይጠቅማችኋልና፡፡ የትሩፋትንም ባለቤት ሁሉ ችሮታውን (ምንዳውን) ይሰጠዋል፡፡ ብትሸሹም እኔ በእናንተ ላይ የታላቁን ቀን ቅጣት እፈራላችኋለሁ፡፡

መመለሻችሁ ወደ አላህ ብቻ ነው፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

ንቁ! እነሱ ከእርሱ (ከአላህ) ይደበቁ ዘንድ ደረቶቻቸውን ያጥፋሉ፡፡ ንቁ! ልብሶቻቸውን በሚከናነቡ ጊዜ የሚደብቁትን የሚገልጹትንም ሁሉ ያውቃል፡፡ እርሱ በደረቶች ውስጥ ያለውን ሁሉ ዐዋቂ ነውና፡፡