islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


(አባቱም) አለ «ልጄ ሆይ! ሕልምህን ለወንድሞችህ አታውራ፡፡ ላንተ ተንኮልን ይሰሩብሃልና፡፡ ሰይጣን ለሰው ግልጽ ጠላት ነውና፡፡»

«እንደዚሁም (እንዳየኸው) ጌታህ ይመርጥሃል፡፡ ከንግግሮችም ፍች ያስተምርሃል፡፡ ጸጋውንም ከአሁን በፊት በሁለቱ አባቶችህ በኢብራሂምና በኢስሐቅ ላይ እንዳሟላት በአንተ ላይና በያዕቆብ ዘሮችም ላይ ይሞላታል፡፡ ጌታህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡»

በዩሱፍና በወንድሞቹ (ታሪኮች) ውስጥ ለጠያቂዎች ሁሉ በእርግጥ አስደናቂ ምልክቶች ነበሩ፡፡

(ወንድሞቹ) ባሉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ «እኛ ጭፍሮች ስንሆን ዩሱፍና ወንድሙ (ብንያም) ወደ አባታችን ከእኛ ይበልጥ የተወደዱ ናቸው፡፡ አባታችን በግልጽ ስህተት ውስጥ ነው፡፡

«ዩሱፍን ግደሉ፡፡ ወይም በ(ሩቅ) ምድር ላይ ጣሉት፡፡ ያባታችሁ ፊት ለእናንተ የግል ይኾናልና፡፡ ከእርሱም በኋላ መልካም ሕዝቦች ትሆናላችሁና» (ተባባሉ)፡፡

ከእነሱ አንድ ተናጋሪ «ዩሱፍን አትግደሉ ግን በጉድጓድ አዘቅት ጨለማ ውስጥ ጣሉት፤ ከተጓዢዎች አንዱ ያነሳዋልና፡፡ ሠሪዎች ብትኾኑ (በዚሁ ተብቃቁ) አላቸው፡፡

(እነሱም) አሉ «አባታችን ሆይ! በዩሱፍ ላይ ለምን አታምነንም እኛም ለእርሱ በእርግጥ አዛኞች ነን፡፡»

«ነገ ከእኛ ጋር ላከውና ይደሰት፤ ይጫወትም፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎች ነን፡፡»

«እኔ እርሱን (ዩሱፍን) ይዛችሁ መሌዳችሁ በእርግጥ ያሳዝነኛል፡፡ እናንተም ከእርሱ ዘንጊዎች ስትሆኑ ተኩላ ይበላዋል ብዬ እፈራለሁ» አላቸው፡፡

«እኛ ጭፍራዎች ሆነን ሳለን ተኩላ ቢበላውማ እኛ ያን ጊዜ በእርግጥ ከሳሪዎች ነን» አሉት፡፡