islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


ነፍስህንም፤ ከእነዚያ ጌታቸውን ፊቱን (ውዴታውን) የሚሹ ኾነው በጧትና በማታ ከሚግገዙት ጋር አስታግስ፡፡ የቅርቢቱንም ሕይወት ሽልማት የምትሻ ሆነህ ዓይኖችህ ከእነሱ (ወደ ሌላ) አይለፉ፡፡ ልቡንም እኛን ከማስታወስ ያዘነጋነውን ፍላጎቱንም የተከተለውን ነገሩም ሁሉ ወሰን ማለፍ የሆነውን ሰው አትታዘዝ፡፡

«እውነቱም ከጌታችሁ ነው፡፡ የሻም ሰው ይመን፤ የሻም ሰው ይካድ» በላቸው፡፡ እኛ ለበደለኞች አጥሯ በእነሱ የከበበ የኾነችውን እሳት አዘጋጅተናል፡፡ (ከጥም) እርዳታንም ቢፈልጉ እንደ ዘይት ዝቃጭ ባለ ፊቶችን በሚጠብስ ውሃ ይረዳሉ፡፡ መጠጡ ከፋ! መደገፊያይቱም ምንኛ አስከፋች!

እነዚያ ያመኑና መልካም ሥራዎችንም የሠሩ እኛ ሥራን ያሳመረን ሰው ምንዳ አናጠፋም፡፡

እነዚያ ለእነሱ የመኖሪያ ገነቶች ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው አሏቸው፡፡ በእርሷ ውስጥ ከወርቅ የኾኑን አንባሮች ይሸለማሉ፡፡ ከቀጭን ሐርና ከወፍራም ሐርም አረንጓዴን ልብሶች ይለብሳሉ፡፡ በውስጧ በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ የተደገፉ ኾነው (ይቀመጣሉ)፡፡ ምንዳቸው ምን ያምር! መደገፊያይቱም ምንኛ አማረች!

ለእነሱም የሁለትን ሰዎች ምሳሌ ግለጽላቸው፡፡ ለአንደኛቸው (ለከሓዲው) ከወይኖች የኾኑን ሁለት አትክልቶች አደረግንለት፡፡ በዘምባባም አከበብናቸው፡፡ በመካከላቸውም አዝመራን አደረግን፡፡

ሁለቱም አትክልቶች ሰብላቸውን ሰጡ፡፡ ከእርሱም ምንም አላጎደሉም፡፡ በመካከላቸውም ወንዝን አፈሰስን፡፡

ለእርሱም (ከአትክልቶቹ ሌላ ፍሬያማ) ሀብት ነበረው፡፡ ለጓደኛውም (ለአማኙ) እርሱ የሚወዳደረው ሲኾን «እኔ ካንተ በገንዘብ ይበልጥ የበዛሁ በወገንም ይበልጥ የበረታሁ ነኝ» አለው፡፡