islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


የመጽሐፉን ባለቤቶችም በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው ክርክር እንጂ አትከራከሩ፡፡ ከእነርሱ እነዚያን የበደሉትን ሲቀር፡፡ በሉም «በዚያ ወደኛ በተወረደው ወደናንተም በተወረደው አመንን፡፡ አምላካችንም አምላካችሁም አንድ ነው፡፡ እኛም ለእርሱ ታዛዦች ነን፡፡»

እንደዚሁም ወዳንተ መጽሐፍን አወረድን፡፡ እነዚያም መጽሐፍን የሰጠናቸው፤ በእርሱ ያምናሉ፡፡ ከእነዚህም (ከመካ ሰዎች) በእርሱ የሚያምኑ አልሉ፡፡ በተዓምራቶቻችንም ከሓዲዎቹ እንጂ ማንም አይክድም፡፡

ከእርሱ በፊትም መጽሐፍን የምታነብ በቀኝህም የምትጽፈው አልነበርክም፡፡ ያን ጊዜ አጥፊዎቹ በእርግጥ በተጠራጠሩ ነበር፡፡

አይደለም እርሱ (ቁርኣን) በእነዚያ ዕውቀትን በተሰጡት ሰዎች ልቦች ውስጥ (የጠለቀ) ግልጾች አንቀጾች ነው፡፡ በአንቀጾቻችንም በዳዮቹ እንጂ ሌላው አይክድም፡፡

«በእርሱ ላይም ከጌታህ ዘንድ ተዓምራቶች ለምን አልተወረዱም» አሉ፡፡ «ተዓምራቶች አላህ ዘንድ ብቻ ናቸው፡፡ እኔም ግልጽ አስፈራሪ ብቻ ነኝ» በላቸው፡፡

እኛ መጽሐፉን በእነሱ ላይ የሚነበብ ኾኖ ባንተ ላይ ማውረዳችን አይበቃቸውምን በዚህ ውስጥ ለሚያምኑ ሕዝቦች ችሮታና ግሳጼ አለበት፡፡

«በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ በአላህ በቃ፡፡ በሰማያትና በምድርም ያለውን ሁሉ ያውቃል» በላቸው፡፡ እነዚያም በብላሽ ነገር ያመኑ በአላህም የካዱ እነዚያ እነሱ ከሳሪዎች ናቸው፡፡