islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


ዕውሩና የሚያየውም አይስተካከሉም፡፡

ጨለማዎችና ብርሃንም፤ (እንደዚሁ)፡፡

ጥላና ሐሩርም፡፡

ሕያዋንና ሙታንም አይስተካከሉም፡፡ አላህ የሚሻውን ሰው ያሰማል፡፡ አንተም በመቃብር ውስጥ ያሉትን አሰሚ አይደለህም፡፡

አንተ አስጠንቃቂ እንጂ ሌላ አይደለህም፡፡

እኛ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን በእውነቱ (መምሪያ) ላክንህ፡፡ ማንኛይቱም ሕዝብ በውስጧ አስፈራሪ ያላለፈባት የለችም፡፡

ቢያስተባብሉህም እነዚያ ከበፊታቸው የነበሩት በእርግጥ አስተባብለዋል፡፡ መልክተኞቻቸው በግልጽ ማስረጃዎችን፣ በጽሑፎችም፣ አብራሪ በኾነ መጽሐፍም መጥተዋቸዋል፡፡

ከዚያም እነዚያን የካዱትን ያዝኳቸው፡፡ ቅጣቴም እንዴት ነበር! (በስፍራው ነው)፡፡

አላህ ከሰማይ ውሃን ማውረዱን አላየህምን? በእርሱም ዓይነቶቻቸው የተለያዩ ፍሬዎችን አወጣን፡፡ ከጋራዎችም መልኮቻቸው የተለያዩ ነጮች፣ ቀዮችም፣ በጣም ጥቁሮችም የኾኑ መንገዶች አልሉ፡፡

ከሰዎችም፣ ከተንቀሳቃሾችም፣ ከቤት እንሰሳዎችም እንደዚሁ መልኮቻቸው የተለያዩ አልሉ፡፡ አላህን ከባሮቹ ውስጥ የሚፈሩት ዐዋቂዎቹ ብቻ ናቸው፡፡ አላህ አሸናፊ መሓሪ ነው፡፡

እነዚያ የአላህን መጽሐፍ የሚያነቡ፣ ሶላትንም አስተካክለው ያደረሱ፣ ከሰጠናቸውም ሲሳይ በምስጢርም ኾነ በግልጽ የለገሱ፣ በፍጹም የማትከስርን ንግድ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

ምንዳዎቻቸውን ሊሞላላቸው፣ ከችሮታውም ሊጨምርላቸው (ተስፋ ያደርጋሉ)፡፡ እርሱ በጣም መሓሪ አመስጋኝ ነውና፡፡