islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


እነዚያ «ጌታችን አላህ ነው» ያሉ ከዚያም ቀጥ ያሉ «አትፍሩ፤ አትዘኑም፤ በዚያችም ተስፋ ቃል ትደረግላችሁ በነበራችሁት ገነት ተበሰሩ» በማለት በነሱ ላይ መላእክት ይወርዳሉ፡፡

«እኛ በቅርቢቱም ሕይወት በመጨረሻይቱም ረዳቶቻችሁ ነን! ለእናንተም በእርሷ ውስጥ ነፍሶቻችሁ የሚሹት ሁሉ አልላችሁ፡፡ ለእናንተም በእርሷ ውስጥ የምትፈልጉት ሁሉ አልላችሁ፡፡

«መሓሪ አዛኝ ከኾነው አላህ መስተንግዶ ሲኾን» (ይባላሉ)፡፡

ወደ አላህ ከጠራና መልካምንም ከሠራ፣ «እኔ ከሙስሊሞች ነኝ» ካለም ሰው ይበልጥ ቃሉ ያማረ ማን ነው?

መልካሚቱና ክፉይቱም (ጸባይ) አይተካከሉም፡፡ በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው ጸባይ (መጥፎይቱን) ገፍትር፡፡ ያን ጊዜ ያ ባንተና በእርሱ መካከል ጠብ ያለው ሰው እርሱ ልክ እንደ አዛኝ ዘመድ ይኾናል፡፡

(ይህችንም ጠባይ) እነዚያ የታገሱት እንጅ ሌላው አያገኛትም፡፡ የትልቅም ዕድል ባለቤት እንጅ ማንም አይገጠማትም፡፡

ከሰይጣንም ጉትጎታ ቢያገኝህ (ከመልካም ጠባይም ቢመልስህ) በአላህ ተጠበቅ፡፡ እነሆ እርሱ ሰሚው ዐዋቂው ነውና፡፡

ሌሊትና ቀንም ፀሐይና ጨረቃም ከምልክቶቹ ናቸው፡፡ ለፀሐይና ለጨረቃ አትስገዱ፡፡ ለእዚያም ለፈጠራቸው አላህ ስገዱ፡፡ እርሱን ብቻ የምትግገዙ እንደ ኾናችሁ (ለሌላ አትስገዱ)፡፡

ቢኮሩም እነዚያ በጌታህ ዘንድ ያሉት (መላእክት) በቀንም በሌሊትም ለእርሱ ያወድሳሉ፡፡ እነርሱም አይሰለቹም፡፡