islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


ዓይኖቻቸው ያቀረቀሩ ኾነው፤ ፍጹም የተበተነ አንበጣ መስለው ከመቃብሮቹ ይወጣሉ፡፡

ወደ ጠሪው አንገቶቻቸውን ሳቢዎች ቸኳዮች ኾነው (ይወጣሉ)፡፡ ከሓዲዎቹ (ያን ጊዜ ምን ይላሉ?) «ይህ ብርቱ ቀን ነው» ይላሉ፡፡

ከእነርሱ በፊት የኑሕ ነገድ አስተባበለች፡፡ ባሪያችንንም (ኑሕን) አስተባበሉ፡፡ «ዕብድ ነውም» አሉ፡፡ ተገላመጠም፡፡

ጌታውንም «እኔ የተሸነፍኩ ነኝና እርዳኝ» ሲል ጠራ፡፡

ወዲያውም የሰማይን ደጃፎች በሚንቧቧ ውሃ ከፈትን፡፡

የምድርንም ምንጮች አፈነዳን፡፡ ውሃውም (የሰማዩና የምድሩ) በእርግጥ በተወሰነ ኹነታ ላይ ተገናኘ፡፡

ባለ ሳንቃዎችና ባለሚስማሮች በኾነችም ታንኳ ላይ ጫንነው፡፡

በጥበቃችን ስር ኾና ትንሻለላለች፡፡ ተክዶ ለነበረው ሰው ምንዳ (ይህንን ሠራን)፡፡

ተዓምር አድርገንም በእርግጥ ተውናት፡፡ ከተገሳጭም አልለን?

ቅጣቴና ማስጠንቀቂያዎቼም እንዴት ነበሩ?

ቁርኣንንም ለመገንዘብ በእርግጥ አገራነው፡፡ ተገንዛቢም አልለን?

ዓድ አስተባበለች፡፡ ቅጣቴና ማስጠንቀቂያዎቼም እንዴት ነበሩ!

እኛ በእነርሱ ላይ ዘወትር መናጢ በኾነ ቀን በኀይል የምትንሻሻ ነፋስን ላክንባቸው፡፡

ሰዎቹን ልክ ከሥሮቻቸው የተጎለሰሱ የዘንባባ ግንዶች መስለው (ከተደበቁበት) ትነቅላቸዋለች፡፡

ቅጣቴና ማስጠንቀቂያዎቼም እንዴት ነበሩ?

ቁርኣንንም ለማስታወስ በእርግጥ አገራነው፡፡ ተገሳጭም አልለን?

ሰሙድ በአስፈራሪዎቹ አስተባበለች፡፡

«ከእኛ የኾነን አንድን ሰው እንከተለዋለን? እኛ ያን ጊዜ በስህተትና በዕብደት ውስጥ ነን» አሉ፡፡

«ከኛ መካከል በእርሱ ላይ (ብቻ) ማስገንዘቢያ (ራእይ) ተጣለለትን? አይደለም እርሱ ውሸታም ኩሩ ነው» (አሉ)፡፡

ውሸታሙ ኩሩው ማን እንደኾነ ነገ በእርግጥ ያውቃሉ፡፡

እኛ ሴት ግመልን ለእነርሱ መፈተኛ ትኾን ዘንድ ላኪዎች ነን፡፡ ተጠባበቃቸውም፡፡ ታገስም፡፡