islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


አንተ ነቢዩ ሆይ! አላህን ፍራ፡፡ ከሓዲዎችንና መናፍቃንንም አትታዘዝ፡፡ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡

ከጌታህም ወደ አንተ የሚወረደውን ተከተል፡፡ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውሰጠ አዋቂ ነውና፡፡

በአላህም ላይ ተመካ፡፡ መመኪያም በአላህ በቃ፡፡

አላህ ለአንድ ሰው በሆዱ ውስጥ ሁለትን ልቦች አላደረገም፡፡ ሚስቶቻችሁንም እነዚያን ከእነርሱ እንደናቶቻችሁ ጀርባዎች ይሁኑብን የምትሏቸውን እናቶቻችሁ አላደረገም፡፡ ልጅ በማድረግ የምታስጠጓቸውንም ልጆቻችሁ አላደረገም፡፡ ይህ በአፎቻችሁ የምትሉት ነው፡፡ አላህም እውነቱን ይናገራል፡፡ እርሱም ትክክለኛውን መንገድ ይመራል፡፡

ለአባቶቻቸው (በማስጠጋት) ጥሯቸው፡፡ እርሱ አላህ ዘንድ ትክክለኛ ነው፡፡ አባቶቻቸውንም ባታውቁ በሃይማኖት ወንድሞቻችሁና ዘመዶቻችሁ ናቸው፡፡ በእርሱ በተሳሳታችሁበት ነገርም በእናንተ ላይ ኀጢአት የለባችሁም፡፡ ግን ልቦቻችሁ ዐውቀው በሠሩት (ኀጢአት አለባችሁ)፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡

ነቢዩ በምእምናን ከነፍሶቻቸው ይበልጥ ተገቢ ነው፡፡ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው፡፡ የዝምድና ባለቤቶችም ከፊላቸው በከፊሉ (ውርስ) በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ከምእምናንና ከስደተኞቹ ይልቅ የተገባቸው ናቸው፡፡ግን ወደ ወዳጆቻችሁ (በኑዛዜ) መልካምን ብትሰሩ (ይፈቀዳል)፡፡ ይህ በመጽሐፉ ውሰጥ የተመዘገበ ነው፡፡