islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


ይጠይቁሃል በላቸው፡- «ወላጅና ልጅ ሳይኖረው በሚወረስ ሰው አላህ ይነግራችኋል፡፡ ለእርሱ ልጅ የሌለው ሰው ቢሞት ለእርሱም እኅት ብትኖረው ለእርስዋ ከተወው ረጀት ግማሹ አላት፡፡ እርሱም ለርሷ ልጅ የሌላት እንደኾነች (በሙሉ) ይወርሳታል፡፡ ሁለት (እኅቶች ወይም ከሁለት በላይ) ቢኾኑም ከተወው ረጀት ከሦስት ሁለት እጁ አላቸው፡፡ ወንድሞች (ና እኅቶች) ወንዶችና ሴቶች ቢኾኑም ለወንዱ የሁለት ሴቶች ድርሻ ብጤ አለው፡፡ አላህ እንዳትሳሳቱ ለእናንተ ያብራራል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡»

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በቃል ኪዳኖች ሙሉ፡፡ በእናንተ ላይ የሚነበበው ብቻ ሲቀር፡፡ የግመል፣ የከብት፣ የበግና የፍየል እንስሳዎች እናንተ በሐጅ ሥራ ላይ ኾናችሁ ማደንን የተፈቀደ ሳታደረጉ ለእናንተ ተፈቀዱ፡፡ አላህ የሚሻውን ይፈርዳል፡፡

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የአላህ (ክልክል ያደረጋቸውን) ምልክቶች የተፈቀዱ አታድርጉ፡፡ የተከበረውንም ወር በመጋደል አትድፈሩ፡፡ ወደ መካ የሚነዱትን መስዋዕትና የሚታበቱባቸውንም ገመዶች ከጌታቸው ችሮታንና ውዴታን ፈልገው ወደ ተከበረው ቤት አሳቢዎችንም ሰዎች (አትንኩ)፡፡ ከሐጅም ሥራ በወጣችሁ ጊዜ ዐድኑ፡፡ ከተከበረው መስጊድ ስለከለከሉዋችሁ ሰዎችን መጥላትም (በነሱ ላይ) ወሰን እንድታልፉ አይገፋፋችሁ፡፡ በበጎ ነገርና አላህን በመፍራትም ተረዳዱ፡፡ ግን በኃጢአትና ወሰንን በማለፍ አትረዳዱ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡