islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


የአላህ መልክተኛ ሙሐመድ እነዚያም ከእርሱ ጋር ያሉት (ወዳጆቹ) በከሓዲዎቹ ላይ ብርቱዎች በመካከላቸው አዛኞች ናቸው፡፡ አጎንባሾች፣ ሰጋጆች ኾነው ታያቸዋለህ፡፡ ከአላህ ችሮታንና ውዴታን ይፈልጋሉ፡፡ ምልክታቸው ከስግደታቸው ፈለግ ስትኾን በፊቶቻቸው ላይ ናት፡፡ ይህ በተውራት (የተነገረው) ጠባያቸው ነው፡፡ በኢንጂልም ውስጥ ምሳሌያቸው ቀንዘሉን አንደአወጣ አዝመራና፣ (ቀንዘሉ) እንዳበረታው፣ እንደወፈረምና፣ ገበሬዎቹን የሚያስደንቅ ኾኖ በአገዳዎቹ ላይ ተስተካክሎ እንደ ቆመ (አዝመራ) ነው፡፡ (ያበረታቸውና ያበዛቸው) ከሓዲዎችን በእነርሱ ሊያስቆጭ ነው፡፡ አላህም እነዚያን ያመኑትንና ከእነርሱ በጎዎችን የሠሩትን ምሕረትንና ታላቅ ምንዳን ተስፋ አድርጎላቸዋል፡፡

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው ፊት (ነፍሶቻችሁን) አታስቀድሙ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ሰሚ ዐዋቂ ነውና፡፡

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ድምጾቻችሁን ከነቢዩ ድምጽ በላይ ከፍ አታድርጉ፡፡ ከፊላችሁም ለከፊሉ እንደሚጮህ በንግግር ለርሱ አትጩሁ፡፡ እናንተ የማታውቁ ስትኾኑ ሥራዎቻችሁ እንዳይበላሹ (ተከልከሉ)፡፡

እነዚያ በአላህ መልክተኛ ዘንድ ድምጾቻቸውን ዝቅ የሚያደርጉ እነዚህ እነዚያ አላህ ልቦቻቸውን ለፍርሃት የፈተናቸው ናቸው፡፡ ለእነርሱም ምሕረትና ታላቅ ምንዳ አላቸው፡፡

እነዚያ ከክፍሎቹ ውጭ ኾነው የሚጠሩህ አብዛኞቻቸው አያውቁም፡፡