islamkingdomfaceBook islamkingdomtwitter islamkingdomyoutube islamkingdomnew


እንደዚሁም «ከመካከላችን አላህ የለገሰላቸው እነዚህ ናቸውን» ይሉ ዘንድ ከፊላቸውን በከፊሉ ሞከርን፡፡ አላህ አመስጋኞቹን ዐዋቂ አይደለምን

እነዚያም በተአምራታችን የሚያምኑት (ወደ አንተ) በመጡ ጊዜ «ሰላም በእናንተ ላይ ይኹን፡፡ ጌታችሁ በነፍሱ ላይ እዝነትን ጻፈ፡፡ እነሆ ከእናንተ ውስጥ በስሕተት ክፉን ሥራ የሠራ ሰው ከዚያም ከእርሱ በኋላ የተጸጸተና ሥራውን ያሳመረ እርሱ (አላህ) መሓሪ አዛኝ ነው» በላቸው፡፡

እንደዚሁም (እውነቱ እንዲገለጽና) የወንጀለኞችም መንገድ ትብራራ ዘንድ አንቀጾችን እንገልጻለን፡፡

«እኔ እነዚያን ከአላህ ሌላ የምትጠሩዋቸውን ከመገዛት ተከልክያለሁ» በላቸው፡፡ «ዝንባሌያችሁን አልከተልም፡፡ ያን ጊዜ በእርግጥ ተሳሳትኩ፡፡ እኔም ከተመሪዎቹ አይደለሁም» በላቸው፡፡

«እኔ ከጌታዬ በኾነች ግልጽ ማስረጃ ላይ ነኝ፡፡ በእርሱም አስተባበላችሁ፡፡ በርሱ የምትቻኮሉበት ቅጣት እኔ ዘንድ አይደለም፡፡ ፍርዱ ለአላህ ብቻ ነው፡፡ እውነትን ይፈርዳል፡፡ እርሱም ከፈራጆች ሁሉ በላጭ ነው» በላቸው፡፡

«በእርሱ የምትቻኮሉበት ቅጣት እኔ ዘንድ በኾነ ኖሮ በእኔና በእናንተ መካከል ነገሩ (ቅጣታችሁ) በተፈጸመ ነበር፡፡ አላህም በደለኞችን ዐዋቂ ነው» በላቸው፡፡

የሩቅ ነገርም መክፈቻዎች እርሱ ዘንድ ናቸው፡፡ ከእርሱ በቀር ማንም አያውቃቸውም፡፡ በየብስና በባሕር ያለውንም ሁሉ ያውቃል፡፡ ከቅጠልም አንዲትም አትረግፍም የሚያውቃት ቢኾን እንጅ፡፡ ከቅንጣትም በመሬት ጨለማዎች ውስጥ የለም ከእርጥብም ከደረቅም አንድም የለም ግልጽ በኾነው መጽሐፍ ውሰጥ (የተመዘገበ) ቢኾን እንጅ፡፡